top of page

ሰሜን ካሊፎርኒያ ኔቫዳ እና አሪዞና ሀገረ ስብከት | EOTC N. CaNvAz Diocese

ዜና

በሰ/ካ/ኔ/አ/ሀ/ስ የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ ክፍል አስተባባሪነት የሰንበት ትምህርት ቤት መምህራን ሥልጠና ተጀመረ
“ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ፡ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ።" (ማርቆስ 16:15)
በሀገረ ስብከታችን የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ ክፍል አስተባባሪነት ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀው የሰንበት ትምህርት ቤት መምህራን ሥልጠና በትናንትናው ምሽት (ሐምሌ 9 ቀን 2018 ዓ.ም) በሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ስብሐት አባ ኃይለ ኢየሱስ ገሠሠ ቡራኬ ተጀምሯል።
የሀገረ ስብከቱ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ ክፍል ለሠልጣኞች የእንኳን ደኅና መጣችሁ መልእክት ባስተላለፈበት ወቅት እንደተገለጸው በእግዚአብሔር ፈቃድና እርዳታ በሀገረ ስብከታችን ሲካሄድ የመጀመሪያው የሆነው ይህ የመምህራን ሥልጠና በመላው ሀገረ ስብከታችን ያሉ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ለሕጻናት፣ ለአዳጊያንና ለወጣቶች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖትን መሠረታዊ አስተምህሮ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸውና እንደየዕድሜያቸው ደረጃ ሊረዱት በሚችሉት መንገድ ወጥነት ባለው መልኩ ለማስተማር ይቻል ዘንድ በየአጥቢያው በቂ መምህራን እንዲኖሩ ታስቦ የተዘጋጀ ነው። በመጀመሪያው ዙር ሥልጠና ከመላው ሀገረ ስብከት የተውጣጡ 142 ሠልጣኞችን የሚያሳትፍና ቀጣይነት ያለው መሆኑ ተገልጿል።
ወጥነት ያለው የሰ/ት/ቤቶች ትምህርት ቤቶች ሥርዓተ ትምህርት የማስተግበሩ ዐላማ በሁሉም አጥቢያዎች ለሕጻናት ለአዳጊያንና ለወጣቶች ተመሳሳይ የትምህርት መርሐ ግብር እንዲሰጥ ከማስቻሉም በላይ ወላጆች በተለያዩ ምክንያቶች የሚኖሩበትን አድራሻ መቀየር ቢኖርባቸው በሀገረ ስብከቱ ውስጥ በአቅራቢያቸው በሚገኝ አጥቢያ ሰንበት ትምህርት ቤት ልጆቻቸውን በመላክ ትምህርታቸው ሳይቋረጥ እንዲከታተሉ የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።
የሀገረ ስብከቱ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ ክፍል ወጥነት ያለው የሰ/ት/ቤቶች ትምህርት ቤቶች ሥርዓተ ትምህርት ለማስተግበር የተነሳበት ምክንያት በአሁኑ ወቅት በመላው ሀገረ ስብከት በሁሉም አጥቢያዎች ለሕጻናት፣ ለአዳጊያንና ለወጣቶች እየተሰጠ ያለው የሃይማኖት ትምህርት አሰጣጥ ሥርዓት ላይ ጥናት በማድረግ በአብዛኞቹ አጥቢያዎች በሀገረ አሜሪካ የተወለዱ ወይም የሚያድጉ ልጆችን ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ ወጥነት ያለው ተከታታይ የሃይማኖት ትምህርት በተመሳሳይ መልኩ በበቂ ሁኔታ እየተሰጠ አለመሆኑን በመገንዘብ ችግሩን ሊቀርፍ ወይም ወደ ተሻለ ደረጃ ሊያደርሰው የሚችል ግብ በማስቀመጥ መሆኑ በመክፈቻው ላይ ተገልጿል።
ፕሮጀክቱን ለማስተግበርም በሀገረ ስብከት ደረጃ ከሦስቱም ወረዳዎች (ስቴቶች) የተውጣጡ በሕጻናትና ወጣቶች ትምህርት ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ ያላቸውን የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትና መምህራን ያካተተ በሀገረ ስብከታችን ሥራ አስኪያጅ የሚመራ ዐቢይ ኮሚቴ ተቋቁሞ ባለፉት ወራት በርካታ ዝግጅቶችን ሲያከናውን መቆየቱ የተገለጸ ሲሆን የሥርዓተ ትምህርት ትግበራው በተያዘለት ዕቅድ መሠረት በመጪው የትምህርት ዘመን ከመስከረም 2019 ዓ.ም (September 2026) ጀምሮ በመላው ሀገረ ስብከት ተግባራዊ እንደሚደረግ ይጠበቃል።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
++++++++++++++++++++++++++++++
"Go into all the world and preach the gospel to every creature" (Mark 16:15)
By the grace of God, the first-ever Sunday School Teachers Training Program organized by the Sunday Schools Department of the Ethiopian Orthodox Tewahedo Church Diocese of Northern California, Nevada, and Arizona officially began yesterday evening (July 16, 2026) with the blessing of Mela'ake Sebhat Abba Haile Eyesus Gesese, Executive Director of the Diocese.
The Diocese Sunday Schools Department delivered a welcoming remark to the trainees, stating that the training aims to prepare qualified Sunday School teachers who can teach the fundamental doctrines of the Ethiopian Orthodox Tewahedo Faith to children, adolescents, and youth in their native language and according to their age level, using a standardized curriculum. The first training cohort includes 142 participants from across the Diocese.
The standardized curriculum is expected to be implemented in all parishes beginning of September 2026, helping ensure consistent instruction. Under this system, children will be able to continue their religious education seamlessly by attending Sunday School of another parish within the Diocese, in the event families may relocate.
The Diocese launched this initiative after recognizing the need for a more consistent and age-appropriate Orthodox Tewahedo Christian education across its parishes, particularly for children growing up in the United States.
Under the leadership of the Executive Director of the Diocese, a Steering Committee, composed of distinguished clergy, scholars, and Sunday School teachers from all three states of the Diocese who have extensive experience in children's and youth education, have spent the past several months preparing the project.
Glory be to God.

የ2018 ዓ.ም (2026 GC) የሰንበት ትምህርት ቤቶች ቀን በሰሜን ካሊፎርኒያ፣ ኔቫዳና አሪዞና ሀገረ ስብከት ሐሙስ ሐምሌ 2 ቀን 2018 ዓ.ም (July 9th, 2026) በልዩ ልዩ መርሐ ግብሮች በቨርቹዋል ጉባኤ በደማቅ ሁኔታ ተከበረ።
የ2018 ዓ.ም (2026 GC) የሰንበት ትምህርት ቤቶች ቀን በሰሜን ካሊፎርኒያ፣ ኔቫዳና አሪዞና ሀገረ ስብከት ሐሙስ ሐምሌ 2 ቀን 2018 ዓ.ም (July 9th, 2026) በልዩ ልዩ መርሐ ግብሮች በቨርቹዋል ጉባኤ በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል።
ክቡር መልአከ ስብሐት አባ ኃይለኢየሱስ ገሠሠ የሀገረ ስብከታችን ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የላስቬጋስ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል አስተዳዳሪ በጸሎት በመክፈት ቡራኬ በሰጡበት በዚሁ ጉባኤ ላይ ክቡር መጋቤ አእላፍ ቀሲስ ተመስገን ደምሴ የሰሜን ካሊፎርኒያ ወረዳ ሊቀ ካህናትና የሳን ሆዜ ቁልቢ ደብረ ይባቤ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ፣ ዲ/ን ምሥክር ደምሴ፣ የሀገረ ስብከቱ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ ክፍል ኃላፊና የላስ ቬጋስ ሐመረ ኖህ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ እንዲሁም ከመላው ሀገረ ስብከት የተሰባሰቡ የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት ተገኝተዋል።
"በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ትጠብቁ ዘንድ ትጉ" (ኤፌሶን 4፥3) በሚል መሪ ቃል በተከበረው በዚሁ ዓመታዊ ጉባኤ ላይ ለተገኙ ተሳታፊዎች የሀገረ ስብከቱ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ ክፍል ኃላፊ ዲ/ን ምሥክር ደምሴ የእንኳን ደኅና መጣችሁ መልእክታቸውን ባስተላለፉበት ወቅት “የሰ/ት/ቤቶች ቀን ከበዓለ ጰራቅሊጦስ ጋር ተያይዞ በያመቱ እንዲከበር በቅዱስ ሲኖዶስ በተወሰነው መሠረት መገናኘት የነበረብን ግንቦት 23 ቀን 2018 ዓ.ም (31st of May 2026) ቢሆንም የዘንድሮውን የጰራቅሊጦስ ቀን ባከበርንበት ወቅት የሀገረ ስብከታችን በርካታ የሰ/ት/ቤት አባላት ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና ከኮሌጆች የሚመረቁበት ወቅት በመሆኑ ነባራዊ ሁኔታውን ከግምት ውስጥ በማስገባት የሰ/ት/ቤት አገልግሎታችንን ለመዘከርና እግዚአብሔር አምላክ ስለሰጠን የአገልግሎት በረከት በአንድነት እግዚአብሔርን በማመስገን በያመቱ የሚከበረውን የሰ/ት/ቤቶች ቀን ለመዘከር ነው እነሆ ዛሬ ተገናኝተናል” ሲሉ የጉባኤውን ዓላማ ገልጸዋል።
ክቡር መጋቤ አእላፍ ቀሲስ ተመስገን ደምሴ የሰሜን ካሊፎርኒያ ወረዳ ሊቀ ካህናት በጉባኤው ላይ "በአንድ ልብ ስለ ወንጌል ሃይማኖት አብራችሁ እየተጋደላችሁ፥ በአንድ መንፈስ እንድትቆሙ ስለ ኑሮአችሁ እሰማ ዘንድ፥ ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ ኑሩ።" (ፊልጵስዩስ 1:27) በሚል መሪ ቃል በአማርኛ ቋንቋ ትምህርተ ወንጌል ያስተማሩ ሲሆን የሰ/ት/ቤት አባላት በአንድ አጥቢያ ተወስነው ከማገልገል በበለጠ በአንድነትና በፍቅር በማገልገልና አንድነታቸውን በማጽናት የሰ/ት/ቤቶችን አገልግሎት ከፍ ወዳለ ደረጃ በማድረስ ለቤተ ክርስቲያንና ለወገኖቻቸው በርካታ ሥራዎችን በመሥራት ተደራሽ ሊሆኑ እንደሚገባ አባታዊ ምክራቸውን ለግሰዋል። በሀገረ ስብከቱ በርካታ የሰ/ት/ቤት አባላት የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የእንግሊዝኛ ቋንቋ እንደመሆኑ መጠን የሀገረ ስብከቱ የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ ክፍል በሁለቱም ቋንቋዎች አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ ባለው ቁርጠኝነት መሠረት በዲ/ን መሓሪ ወርቁ (ዶ/ር) “ሰላም” በሚል ርእስ በዓሉን የተመለከተ ትምህርተ ወንጌል በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተሰጠ ሲሆን በትምህርቱም የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት ለአገልግሎት መጠራታቸው የቅድስና ሕይወትን ማዕከል ያደረገና በሌሎችም ሕይወት በጎ ተጽዕኖ የሚያሳድር መሆን እንደሚገባው ተገልጿል።
በሀገረ ስብከቱ የሰ/ት/ቤት ማደራጃ ክፍልም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤትን የመዋቅሯ አካል አድርጋ ያቋቋመችበት ዋነኛ ዓላማ ቤተ ክርስቲያን ለሕጻናት፣ ለአዳጊዎችና ለወጣቶች ዕድሚያቸውን የሚመጥን አገልግሎት ለመስጠት እንዲያስችላት፣ ልጆች በቃለ እግዚአብሔር በመታነጽ የቅድስና ሕይወትን እየተለማመዱ የሚያድጉበት መድረክ ለመፍጠር እንደሆነና፣ የሰ/ት/ቤት አገልግሎትና አደረጃጀት ባለፉት በርካታ ዓመታት እንደተቋም ያሳየውን የዕድገት ደረጃ በተለይም በአሁኑ ወቅት የሰ/ት/ቤቶች አንድነት የሁሉንም ሰ/ት/ቤቶች ተሳትፎ ባካተተ መልኩ የማደራጃውን አገልግሎት በተቀላጠፈ ሁኔታ በሁሉም አጥቢያዎች ተደራሽ ለማድረግ መዋቀሩን የሚያሳይ ገለጻ ተሰጥቷል። የሀገረ ስብከቱ የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ በአሁኑ ወቅት እያከናወናቸው ያሉት ዋና ዋና አገልግሎቶችም ተገልጸዋል።
በጉባኤው ማብቂያ ላይም በኢትዮጵያ በአርሲ ክፍለ ሀገር በግፍ ለተገደሉ ክርስቲያኖች የመታሰቢያ ጸሎት ተደርጓል።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
////////////////////////////////////////////////////////////////
The Ethiopian Orthodox Tewahedo Church Diocese of Northern California, Nevada, and Arizona celebrated Sunday Schools Day on July 9, 2026, through a virtual gathering featuring prayers, sermons, presentations, and fellowship.
The event that was opened with prayer by Rev. Mele'ake Sibhat Aba Haileyesus Gesese, Executive Director of the Diocese, and Head of the Las Vegas Debre Mihret St Michael Church, was attended by Rev. Megabe A'elaf Qesis Temesgen Demse, the Northern California Wereda Liqa-Kahinat and a member of the clergy at San Jose Qulbi Debre Yibabe St. Gebriel, Dn. Misikir Demse, the Head of the Diocese Sunday Schools Department, and a member of the clergy at Las Vegas Hamere Noah Kidane Mihret church, as well as Sunday School members from across the Diocese.
Held under the theme, "Endeavoring to keep the unity of the Spirit in the bond of peace" (Ephesians 4:3), the gathering emphasized unity, collaboration, and faithful service. In his welcome address, Deacon Misikir Demse, Head of the Diocese Sunday Schools Department, explained that although Sunday Schools Day is traditionally observed on along with the Feast of Pentecost as directed by the Holy Synod, this year's celebration was postponed because many Sunday School members were graduating from high school and college on the same day.
Rev. Megabe Aelaf Qesis Temesgen Demse delivered an Amharic sermon from Philippians 1:27, encouraging Sunday School members to work together in love and unity beyond their individual parishes to strengthen the Church's mission. Dr. Mehari Worku presented an English sermon titled "Peace," emphasizing that serving in the Sunday School ministry requires a life of holiness and a positive influence on others.
The Diocese Sunday Schools Department also presented the mission, structure, and ongoing initiatives of the Sunday School ministry, highlighting the Church’s commitment to providing age-appropriate Orthodox Tewahedo Christian education and expanding its services throughout all parishes in both Amharic and English. It was also mentioned that the department provides a platform for equal participation of all Sunday Schools through the Sunday Schools Union, which is the implementing arm of the department.
The gathering concluded with a memorial prayer for the Christians who were martyred in the Arsi region of Ethiopia.
Glory be to God.

የጸሎተ ፍትሐት እና ድጋፍ ጥሪ በአርሲ ሀገረ ስብከት ቤተ ክርስቲያን ላይ ለደረሰው ጥቃት እና ለተሰዉ ኦርቶዶክሳውያን
ከኢት/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያን ሰሜን ካሊፎርኒያ ኔቫዳ እና አሪዞና ሀገረ ስብከት ለመላው የሀገረ ስብከቱ አድባራት እና ገዳማት የተላለፈ የጸሎተ ፍትሐት እና የድጋፍ ጥሪ። ጥሪውን ለመመልከት Read more የሚለውን ሊንክ ይጫኑ።

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የሰሜን አሜሪካ ካሪቢያንና ላቲን አሜሪካ አኅጉረ ስብከት የሰንበት ት/ቤቶች ኅብረት 26ኛ ዓመታዊ ጉባዔ በሰሜን ካሊፎርኒያ ኔቫዳ እና አሪዞና ሀገረ ስብከት ፊኒክስ አሪዞና ከተማ ላይ ከነሐሴ 29 እስከ ጳጒሜን 2 ይካሄዳል።
በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የሰሜን አሜሪካ ካሪቢያንና ላቲን አሜሪካ አኅጉረ ስብከት የሰንበት ት/ቤቶች ኅብረት 26ኛ ዓመታዊ ጉባዔ በሰሜን ካሊፎርኒያ ኔቫዳ እና አሪዞና ሀገረ ስብከት ፊኒክስ አሪዞና ከተማ ላይ ከነሐሴ 29 እስከ ጳጒሜን 2 ይካሄዳል። በሀገረ ስብከታችን አጥቢያዎች የምታገለግሉ የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን እና መዘምራት ለጉባዔው ከወዲሁ እንድትዘጋጁ የሀገረ ስብከቱ የሰንበት ት ምህርት ቤቶች ማደራጃ ክፍል ጥሪ ያቀርባል።

ብጹዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ዶ/ር የሰሜን ካሊፎርኒያ ኔቫዳ እና አሪዞና ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በላስ ቬጋስ ደብረ ምህረት ቅ/ሚካኤል የኢት/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያን ግንቦት ፳፫ ቀን ፳፻፲፰ ዓ/ም ለ ፳፫ ደቀ መዛሙርት ሢመተ ዲቁና ሰጡ።
ብጹዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ዶ/ር የሰሜን ካሊፎርኒያ ኔቫዳ እና አሪዞና ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በላስ ቬጋስ ደብረ ምህረት ቅ/ሚካኤል የኢት/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያን ግንቦት ፳፫ ቀን ፳፻፲፰ ዓ/ም ለ ፳፫ ደቀ መዛሙርት ሢመተ ዲቁና ሰጡ። ብጹዕነታቸው በዕለቱ ለወላጆች ባስተላለፉት አባታዊ ቃለ በረከት የክህነት አገልግሎት መመረጥ መሆኑን በመግለጽ ታዳጊዎች ቤተ ክርስቲያንን ተረክበው እንዲያገለግሉ በተቻለው ሁሉ ለክህነት አገልግሎት የሚያስፈልገውን የአብነት ትምህርት እና ተዛማጅ የቤተክርስቲያኒቱን አስተምህሮ እንዲማሩ ማድረግ የወላጆች ድርሻ መሆኑን ገልጸዋል። ብጹዕነታቸው ዕለቱ በዓለ ጰራቅሊጦስ በመሆኑ ቀድሰው በማቁረብ እና አባታዊ ቡራኬ / ቃለ በረከት በማስተላለፍ ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን ፈጽመዋል።

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መዋቅራዊ አሠራር ውጭ የተፈጸመውን ሕገ ወጥ እና ኢ-ቀኖናዊ ድርጊት
ማውገዝን እና መደረግ የሚገባውን ጥንቃቄ በተመለከተ የተላለፈ መግለጫ
የመግለጫውን ሙሉ ቃል ለማንበብ Read More የሚለውን ይጫኑ

በሰሜን ካሊፎርኒያ ኔቫዳ እና አሪዞና ሀገረ ስብከት የኆኅተ ሰማይ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሃንስ ወቅድስት አርሴማ አንድነት ገዳም መንፈሳዊ ኮሌጅ እና የአብነት ምሥክር ጉባዔ ቤት ስርዓተ ትምህርት ሥራ ላይ እንዲውል ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳ ኔ አስተላለፈ።
የውሳኔውን ሙሉ ቃል ለማድመጥ Read More የሚለውን ሊንክ ይጫኑ

በሰሜን ካሊፎርኒያ ኔቫዳ እና አሪዞና ሀገረ ስብከት የኆኅተ ሰማይ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሃንስ ወቅድስት አርሴማ አንድነት ገዳም ያሰራውን ሁለገብ ሁለት ግዙፍ አዳራሽ አስመረቀ።
በሰሜን ካሊፎርኒያ ኔቫዳ እና አሪዞና ሀገረ ስብከት የኆኅተ ሰማይ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሃንስ ወቅድስት አርሴማ አንድነት ገዳም ያሰራውን ሁለገብ ሁለት ግዙፍ አዳራሽ አስመረቀ። በዕለቱ ብጹዕ አቡነ ማርቆስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የዋሽንግተን (ሲያትል)፣ ኦሪገን፣ አይዳሆ እና አከባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ ብጹዕ አቡነቴዎፍሎስ ዶ/ር የሰሜን ካሊፎርኒያ ኔቫዳ እና አሪዞና ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የገዳሙ መሥራች አዳራሾቹን ባርከው መርቀዋል። በዕለቱ የገዳሙ ምሥረታ ሦስተኛ ዓመት በዓል የተከበረ ሲኾን ክብረ በዓሉ ከተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች በመጡ ሰባክያነ ወንጌል ፣ ካህናት ፣ ዘማርያን እና ምዕመናን በድምቀት ተከብሯል።

በሰሜን ካሊፎርኒያ ኔቫዳ እና አሪዞና ሀገረ ስብከት አዲስ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን በኮንትራ ኮስታ ካሊፎርኒያ ተመሠረተ
በሰሜን ካሊፎርኒያ ኔቫዳ እና አሪዞና ሀገረ ስብከት አዲስ አጥቢያ በኮንትራ ኮስታ ካሊፎርኒያ ተመሠረተ። የኮንትራ ኮስታ አካባቢ ነዋሪ ምዕመናን ለሀገረ ስብከቱ ባቀረቡት መጠይቅ መሠረት ሀገረ ስብከቱ በሰሜን ካሊፎርኒያ ወረዳ ቤተ ክህነት መጠይቁን ካጠና እና አስፈላጊውን ቀኖናዊ ማስተካከያ ካደረገ በኋላ በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ዶ/ር መልካም ፈቃድ እና መመሪያ ሰጪነት የምዕመናኑ ጥያቄ ምላሽ አግኝቷል። የአጥቢያው ስያሜም ቅዱስ ዑራኤል የኢት/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያን በኮንትራ ኮስታ ካሊፎርኒያ በሚል ስያሜ ሆኖ ታቦተ ቅዱስ ዑራኤል እና ጊዜያዊው ቤተ ክርስቲያን በብጹዕነታቸው ተባርኮ ቅዳሴ ቤቱ ሚያዝያ 10 ቀን 2018 ዓ/ም ወይም April 18 ተከብሯል።

በሰሜን ካሊፎርኒያ ኔቫዳ እና አሪዞና ሀገረ ስብከት የኆኅተ ሰማይ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሃንስ ወቅድስት አርሴማ አንድነት ገዳም መንፈሳዊ ኮሌጅ እና የአብነት ምሥክር ጉባዔ ቤት እንዲቋቋም ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ሰጠ
በሰሜን ካሊፎርኒያ ኔቫዳ እና አሪዞና ሀገረ ስብከት የኆኅተ ሰማይ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሃንስ ወቅድስት አርሴማ አንድነት ገዳም መንፈሳዊ ኮሌጅ እና የአብነት ምሥክር ጉባዔ ቤት እንዲቋቋም ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ሰጠ። ውሳኔውን ለማድመጥ Read More የሚለውን ሊንክ ይጫኑ

የሰሜን ካሊፎርኒያ ኔቫዳ እና አሪዞና ሀገረ ስብከ ዓመታዊ ሪፖርት በ44ኛው የኢት/ኦ/ተ/ቤ/ክ መንበረ ፓትርያርክ ዓለም አቀፍ አጠቃላይ የሰበካ ጉባዔ ስብሰባ | ጥቅምት 2018 ዓ.ም
ሪፖርቱን ለማድመጥ Read More የሚለውን ሊንክ ይጫኑ

በብጹዕ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቴዎፍሎስ ዶ/ር ርዕሰ መንበርነት የሚመራው የሰሜን ካሊፎርኒያ ኔቫዳ እና አሪዞና ሀገረ ስብከት አምስተኛ ዓመታዊ አጠቃላይ ስብሰባውን አጠናቀቀ።
የስብሰባውን ሙሉ መግለጫ Read more የሚለውን ሊንክ ይጫኑ እና ይመልከቱ

በሰሜን ካሊፎርኒያ ኔቫዳ እና አሪዞና ሀገረ ስብከት የሐመረ ኖኅ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ካቴድራል በላስ ቬጋስ የልማት ማስፋፊያ ፕሮጀክት ዕቅድ ማስፈጸሚያ የሚሆን የቦታ ፈቃድ በክላርክ ካውንቲ ተሰጠ።
በሰሜን ካሊፎርኒያ ኔቫዳ እና አሪዞና ሀገረ ስብከት የሐመረ ኖኅ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ካቴድራል በላስ ቬጋስ የልማት ማስፋፊያ ፕሮጀክት ዕቅድ ማስፈጸሚያ የሚሆን የቦታ ፈቃድ በክላርክ ካውንቲ ተሰጠ። እ ኤ አ 9/17/2025 ውሳኔውን ያገኘው አጀንዳ ቤተ ክርስቲያኗ ለምታከናውናቸው የልማት ማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ትልቅ በር ከፋች እንደሆነ ተገልጿል። ሙሉ የፈቃዱን ዝርዝር ሁኔታ ለመረዳት Read More የሚለውን ሊንክ ይጫኑ

በሰሜን ካሊፎርኒያ ኔቫዳ እና አሪዞና ሀገረ ስብከት የኆኅተ ሰማይ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሃንስ ወቅድስት አርሴማ አንድነት ገዳም በሐዲሳት እና በብሉያት የትርጓሜ ትምህርት መስጠት ጀመረ።
በሰሜን ካሊፎርኒያ ኔቫዳ እና አሪዞና ሀገረ ስብከት የኆኅተ ሰማይ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሃንስ ወቅድስት አርሴማ አንድነት ገዳም በሐዲሳት እና በብሉያት የትርጓሜ ትምህርት መስጠት ጀመረ። ደቀ መዛሙርት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ዶግማ ፣ ቀኖና እና ትውፊቷን በስፋት እና በጥልቀት በዙም የቀጥታ መስመር ይማራሉ።

በሰሜን ካሊፎርኒያ ኔቫዳ እና አሪዞና ሀገረ ስብከት የኆኅተ ሰማይ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሃንስ ወቅድስት አርሴማ አንድነት ገዳም ሁለገብ አዳራሽ በማሰራት ላይ ይገኛል
በሰሜን ካሊፎርኒያ ኔቫዳ እና አሪዞና ሀገረ ስብከት የኆኅተ ሰማይ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሃንስ ወቅድስት አርሴማ አንድነት ገዳም ሁለገብ አዳራሽ በማሰራት ላይ ይገኛል። የገዳሙ ግዙፍ አዳራሽ አሁን ላይ ያለውን የመገልገያ ቦታ ውሱንነት በሰፊው ይቀርፋል ተብሎ የታቀደ ሲሆን ግንባታው ሲጠናቀቅ ለጸበልተኞች ማረፊያ ፣ ለመሰብሰቢያ አዳራሽ ፣ ለሰመር ኮርስ ተማሪዎች ፣ እንዲሁም በበዓላት የመስተንግዶ ቦታ በመሆን ሊያገለግል እንደሚችል በዕቅዱ ተቀምጧል። የዚህ ታላቅ ራዕይ መሪ አባት ብጹዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ዶ/ር ፕሮጀክቱን ለማስፈጸም በሀገረ ስብከታቸው ባሉ አድባራት በመገኘት የገንዘብ ማስተባበር ሥራ እየሰሩ ያለ ሲሆን የፕሮጀክቱ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትም የብጹዕነታቸውን መመሪያ በመቀበል ፕሮጀክቱን ለማስፈጸም ዕለት ዕለት ጥረት እያደረጉ እንደሆነ ለሀገረ ስብከታችን ጽ/ቤት በደረሰን መረጃ ለመረዳት ችለናል።

ብጹዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ዶ/ር የሰሜን ካሊፎርኒያ ኔቫዳ እና አሪዞና ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በላስ ቬጋስ ደብረ ብሥራት ቅ/ገብርኤል የኢት/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያን ካቴድራል ጥቅምት ፲ ቀን ፳፻፲፯ ዓ/ም ለ ፲፬ ደቀ መዛሙርት ሢመተ ዲቁና ሰጡ።
ብጹዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ዶ/ር የሰሜን ካሊፎርኒያ ኔቫዳ እና አሪዞና ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በላስ ቬጋስ ደብረ ብሥራት ቅ/ገብርኤል የኢት/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያን ካቴድራል ጥቅምት ፲ ቀን ፳፻፲፯ ዓ/ም ለ ፲፬ ደቀ መዛሙርት ሢመተ ዲቁና ያከናወኑ ሲሆን ሥርዓተ ቅዳሴውን በመምራት የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻቸውን ባርከው አቁርበዋል።
ብጹዕነታቸው በዕለቱ ለወላጆች ባስተላለፉት አባታዊ ቃለ በረከት የክህነት አገልግሎት መመረጥ መሆኑን ፣ ከእግዚአብሔር መሆኑን እና የቅድስና አገልግሎት መሆኑን በመግለጽ ሕዝብን እና እግዚአብሔርን በቅንነት ከማገልገል የበለጠ ምንም ነገር እንደሌለ አመልክተው ወላጆችን እና ደቀ መዛሙርቱን ያስተማሩ ካህናቱን አመስግነዋል።

የሰሜን ካሊፎርኒያ ኔቫዳ እና አሪዞና ሀገረ ስብከት ፬ኛ ዓመታዊ አጠቃላይ ስብሰባ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ዶ/ር በተገኙበት ተከናወነ።
የሰሜን ካሊፎርኒያ ኔቫዳ እና አሪዞና ሀገረ ስብከት ዓመታዊ አጠቃላይ ስብሰባውን መስከረም ፲ እና ፲፩ ቀን ፳፻፲፯ ዓ/ም በፍኖተ ሎዛ አቡነ ተ/ኃይማኖት የኢት/ኦ/ተ/ቤ/ክ ሳክራሜንቶ በማካሄድ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በመምከር ውሣኔ አሳልፏል የስብሰባ አቋም መግለጫም አውጥቷል።

የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሃንስ ዓመታዊ ንግሥ በዓል በኆኅተ ሰማይ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሃንስ ወቅድስት አርሴማ የኢት/ኦ/ተ/ቤ/ክ አንድነት ገዳም ዛሬ ሰኔ ፳፱ በታላቅ ድምቀት ተከበረ።
የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሃንስ ዓመታዊ ንግሥ በዓል በኆኅተ ሰማይ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሃንስ ወቅድስት አርሴማ የኢት/ኦ/ተ/ቤ/ክ አንድነት ገዳም ዛሬ ሰኔ ፳፱ በታላቅ ድምቀት ተከበረ። ብጹዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ዶ/ር የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ እና የገዳሙ መስራች ፣ ብጹዕ አቡነ ያዕቆብ የጆርጂያ እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ ከተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች የመጡ አበው መነኮሳት ፣ ቀሳውስት ፣ ዲያቆናት ፣ የአድባራት ሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን እና ምዕመናን ከዋዜማው ጀምሮ ተገኝተው በዓሉን በታላቅ መንፈሣዊ ድምቀት አክብረዋል።
የኆኅተ ሰማይ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሃንስ ወቅድስት አርሴማ የኢት/ኦ/ተ/ቤ/ክ አንድነት ገዳም ለብዙዎች መጽናኛ ፣ የሱባዔ ፣ የፈውስ እና የድኅነት ቅዱስ መካን ኾኖ እያገለገለ ያለ ታላቅ የበረከት ቦታ መሆኑን ለሀገረ ስብከቱ ሚዲያ ቃላቸውን የሰጡ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን ገልጸዋል። በዕለቱም ለዲቁና ማዕረግ ለተዘጋጁ ደቀ መዛሙርት የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ዻዻስ ብጹዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ዶ/ር ስለልጣነ ክህነት ሰጥተዋል።
+++++++++++++++++++++++++
#CaNvAz Diocese | ሰኔ ፳፱ ቀን ፳፻፲፮ ዓ.ም U.S.A +++++++++++++++++++++++++

የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ጉባዔ በሰሜን ካሊፎርኒያ በሳን ሆዜ መካነ ራማ ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል ተከበረ ፡፡
በየዓመቱ በበዓለ ሃምሳ /በዓለ ጰራቅሊጦስ/ በሀገር አቀፍና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት በዓል በሰሜን ካሊፎርኒያ ኔቫዳና አሪዞና ሀገረ ስብከት ፤ በሰሜን ካሊፎርኒያ ወረዳ በሳን ሆዜ መካነ ራማ ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል ሰኔ 16 ቀን 2016 ዓ/ም ተከበረ፡፡ በዕለቱ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ክቡር መልአከ ስብሃት ቆሞስ አባ ኃይለ ኢየሱስ በቀጥታ መስመር ተገኝተው ስለ ሰንበት ትምህርት ቤት አንድነት ጥቅምና በአሁኑ ጊዜ በፈተና ላይ ስላለችው ቤተ ክርስቲያን ያለውን ዘርፈ ብዙ አስተዋጽዖ በሠፊው የገለጹ ሲሆን የሀገረ ስብከቱ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች አንድነት ሕብረት ለሀገረ ስብከቱ ሁለንተናዊ ዕድገት የላቀ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል። በመቀጠል የሀገረ ስብከቱ ዋና ጸሐፊ ሊቀ ሥዩማን ቀሲስ ቡሩክ በቀጥታ መስመር ባስተላለፉት መልዕክት በሀገረ ስብከቱ አድባራት ሥር ያሉ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች አንድነታቸውን ለመጠበቅ እና በመንፈሣዊ የአገልግሎት ዕውቀታቸው ልምድ ለመለዋወጥ እንዲሁም የቤተ ክርስቲያንን ጉዳይ ማዕከል ባደረጉ የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ለመወያየትና ለመመካከር ቋሚ የሩብ ዓመት ወይም የግማሽ ዓመት ግንኙነት ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል። በተጨማሪም የሀገረ ስብከቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ጥበባት ቀሲስ ተገኑ እንዲሁም የወረዳው ሊቀ ካህናት መጋቤ አእላፍ ቀሲስ ተመስገን በጉባዔው ተገኝተው በሰንበት ት/ት ቤት አገልግሎት ዙሪያ ሠፊ ምክር እና መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን ፤ የዕለቱ ተጋባዥ መምህር እና የሀገረ ስብከቱ የስብከተ ወንጌል ኀላፊ ቀሲስ አሉላ ዕለቱንና በዓሉን መነሻ በማድረግ “በአንድ ልብ ነበሩ” (ሐዋ 2፡1) በሚል ርዕስ የሰንበት ት/ቤት አገልጋዮችን አንድነትን የሚመለከት ትምህርት ሠፊ የአገልግሎት ትምህርት ተሰጥቷል። በመጨረሻም በሰሜን ካሊፎርኒያ ወረዳ ቤ/ክህነት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ተወካይ መዘምርት ሠናይት አስተባባሪነት ለተደረገው አገልግሎት እና ከመካነ ራማ ቅ/ገብርኤል ሣንሆዜ እንዲሁም ከደብረ ይባቤ ቅ/ገብርኤል ሣንሆዜ አድባራት በቊጥር ልቀው በጉባዔው ለተገኙ የሰንበት ት/ቤት አባላት በሀገረ ስብከቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ምሥጋና የቀረበ ሲኾን በመዝሙር ፤ በጸበል ጸዲቅ ፤ በምክክርና በወይይት እንዲሁም በኅብረት ጸሎት የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት በዓል በታላቅ ድምቀት ተከብሯል።
+++++++++++++++++++++++++
#CaNvAz Diocese | ሰኔ ፲፮ ቀን ፳፻፲፮ ዓ.ም U.S.A

በዓለ ጰራቅሊጦስ በላስ ቬጋስ ከተማ በደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል የኢት/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያን ካቴድራል
ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ዶ/ር የሰሜን ካሊፎርኒያ ኔቫዳ እና አሪዞና ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በዓለ ጰራቅሊጦስን በላስ ቬጋስ ከተማ በደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል የኢት/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያን ካቴድራል በመገኘት ከመንፈስ ቅዱስ ልጆቻቸው ጋር አከበሩ። በዕለቱ ብጹእነታቸው ቀድሰው በማቁረብ ፣ አባታዊ ቃለ በረከት በማስተላለፍ እና ለኆኅተ ሰማይ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሃንስ ወቅድስት አርሴማ አንድነት ገዳም የጸበል ቤት ማሠሪያ ፕሮጀክት የገንዘብ ድጋፍ በማስተባበር ሐዋርያዊ አገልግሎት ፈጽመዋል። “የትንሣኤውን ኃይል ማወቅ” በሚል ኃይለ ቃል ስለ ክርስቶስ ነገረ ትንሣኤ እና ስለ ትንሣኤው ዓላማ ሠፊ ትምህርት የሰጡ ሲኾን ዕለተ ጰራቅሊጦስ የቤተ ክርስቲያን ልደት ፣ ሁላችን በመንፈስ ቅዱስ የታደስንበት ፣ በመንፈስ ቅዱስ ኃይልን ያገኘንበት ፣ በመንፈስ ቅዱስ ወደ ፊት የምንጓዝበት በመንፈስ ቅዱስ እንደ ሐዋርያት እስከ ሞት ድረስ ራሳችንን ስለ ክርስቶስ አሳልፈን የምንሰጥበት ኃይል የተሰጠበት ዕለት መኾኑን በዓቢይ ቃል አስተምረዋል። በመጨረሻም ከቅዱሳን ሐዋርያት ጋር የነበረ መንፈስ ቅዱስ ዛሬም ቤተ ክርስቲያንን ፣ ሕዝበ ክርስቲያንን ፣ ሀገርን የሚጠብቅ መኾኑን አማኞች እንዲያስተውሉ በማሳሰብ የካቴድራሉ ማህበረ ካህናት እና ምዕመናን ለታላቁ ገዳም የጸበል ቤት ማስፋፊያ ፕሮጀክት በዕለቱ ላደረጉት የገንዘብ አስተዋጽዖ አባታዊ ቃለ በረከት አስተላልፈዋል። ብጹእነታቸው በዚህ ሣምንት የነበራቸውን ሐዋርያዊ አገልግሎት አጠናቀው ምሽቱን ወደ መንበረ ጵጵስናቸው ኆኅተ ሰማይ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሃንስ ወቅድስት አርሴማ አንድነት ገዳም የሚመለሱ ይኾናል።
+++++++++++++++++++++++++
#CaNvAz Diocese | ሰኔ ፲፮ ቀን ፳፻፲፮ ዓ.ም U.S.A

የሰኔ ቅዱስ ሚካኤል ዓመታዊ ንግሥ በዓል በደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤ/ክርስቲያን ኦክላንድ ካሊፎርኒያ
የሰኔ ቅዱስ ሚካኤል ዓመታዊ ንግሥ በዓል በደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤ/ክርስቲያን ኦክላንድ ካሊፎርኒያ ዛሬ ሰኔ ፲፭ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብጹእ አቡነ ቴዎፍሎስ ዶ/ር በተገኙበት በታላቅ ድምቀት ተከብሯል። ብጹእነታቸው ለዲቁና ማዕረግ ለተዘጋጁ ደቀ መዛሙርት ስልጣነ ክህነት በደብሩ የሰጡ ሲኾን ሥርዓተ ቅዳሴውን በመምራት ቀድሰው በማቁረብ የንግሥ በዓሉ ተከናውኗል። በመጨረሻም ብጹእነታቸው አባታዊ ቃለ በረከት እና ቡራኬ አስተላልፈው የበዓሉ መርሐግብር ተጠናቋል።
ምሽቱን ብጹእ አቡነ ቴዎፍሎስ ዶ/ር ወደ ላስ ቬጋስ ለሐዋርያዊ አገልግሎት የሚመለሱ ሲኾን በነገው የጰራቅሊጦስ በዓል በደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል ላስ ቬጋስ በመገኘት በዓሉን ከመንፈስ ቅዱስ ልጆቻቸው ጋር ያከብራሉ።

የቅዱስ ሚካኤል ዓመታዊ ንግሥ በዓል በሐመረ ኖኅ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ካቴድራል ላስ ቬጋስ
የሰኔ ቅዱስ ሚካኤል ዓመታዊ ንግሥ በዓል በላስ ቬጋስ ከተማ በሐመረ ኖኅ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ካቴድራል ላስ ቬጋስ ዛሬ ሰኔ ፲፫ እየተከበረ ይገኛል። የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብጹእ አቡነ ቴዎፍሎስ ዶ/ር ሥርዓተ ቅዳሴውን እየመሩ ቡራኬ የሰጡ ሲኾን ብጹእነታቸው ክብረ በዓሉን እንዳጠናቀቁ ነገ ሰኔ ፲፬ ወደ ኦክላንድ ካሊፎርኒያ ያቀናሉ። በዚህም የቅዱስ ሚካኤል ክብረ በዓል ቅዳሜ ሰኔ ፲፭ በኦክላንድ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ብጹእነታቸው በተገኙበት የሚከበር ይኾናል።
+++++++++++++++++++++++++
#CaNvAz Diocese | ሰኔ ፲፫ ቀን ፳፻፲፮ ዓ.ም U.S.A
+++++++++++++++++++++++++
ከካቴድራሉ በቀጥታ መስመር የሚተላለፈውን የቀጥታ ሥርጭት ለመከታተል ከዚህ ቀጥሎ ያለውን ሊንክ ይጠቀሙ https://www.facebook.com/HamereNoahLV

ሰኔ ፲፪ የቅዱስ ሚካኤል ዓመታዊ ንግሥ በዓል
ሰኔ ፲፪ የቅዱስ ሚካኤል ዓመታዊ ንግሥ በዓል በላስ ቬጋስ ደብረ ምሕረት ቅ/ሚካኤል ቤ/ክርስቲያን ብጹእ አቡነ ቴዎፍሎስ ዶ/ር የሰሜን ካሊፎርኒያ ኔቫዳ እና አሪዞና ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ዶ/ር የኒውዮርክ እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ፣ የሀገረ ስብከቱ የመምሪያ ኃላፊዎች ፣ የአድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ፣ የአድባራት ካህናት ፣ ዲያቆናት ፣ መዘምራን እና በርካታ ምእመናን በተገኙበት በታላቅ ድምቀት እየተከበረ ይገኛል።
ከደብሩ በቀጥታ መስመር የሚተላለፍ የክብረ በዓሉን ቀጥታ ስርጭት ለመከታተል የሚከተለውን ሊንክ ይጠቀሙ፦
https://m.facebook.com/stmichaelvegas/
(#CaNvAz Diocese ሰኔ ፲፪ ቀን ፳፻፲፮ ዓ.ም )

የብጹእ አቡነ ቴዎፍሎስ ሊቀ ጳጳስ ዶ/ር እና የብጹእ አቡነ ጴጥሮስ ዶ/ር ሐዋርያዊ አገልግሎት በላስ ቬጋስ
የሰኔ ቅዱስ ሚካኤል ዓመታዊ ንግሥ በዓል ብጹአን ሊቃነ ጳጳሳት ብጹእ አቡነ ቴዎፍሎስ ሊቀ ጳጳስ ዶ/ር እና የብጹእ አቡነ ጴጥሮስ ዶ/ር በተገኙበት በደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤ/ክርስቲያን ላስ ቬጋስ በታላቅ ድምቀት የተከበረ ሲኾን በቀጣይም ክብረ በዓሉ በላስ ቬጋስ ከተማ በሐመረ ኖኅ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ካቴድራል ላስ ቬጋስ በነገው ዕለት ይከበራል። ዋዜማው ዛሬ ሰኔ ፲፪ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብጹእ አቡነ ቴዎፍሎስ ዶ/ር እና ብጹእ አቡነ ጴጥሮስ የኒውዮርክና አካባቢው ሊቀ ጳጳስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ እንዲሁም የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ስብሃት ቆሞስ አባ ኃይለ ኢየሱስ እና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በተገኙበት እየተከበረ ይገኛል። በመቀጠል ምሽቱን ብጹአን ሊቃነ ጳጳሳቱ በደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ላስ ቬጋስ በመገኘት ካቴድራሉን ጎብኝተዋል በካቴድራሉ የሠርክ ጉባዔ ተገኝተው ቃለ በረከት አስተላልፈዋል።
+++++++++++++++++++++++++
#CaNvAz Diocese | ሰኔ ፲፪ ቀን ፳፻፲፮ ዓ.ም U.S.A

ብጹእ አቡነ ቴዎፍሎስ ዶ/ር የሰሜን ካሊፎርኒያ ኔቫዳ እና አሪዞና ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ለሐዋርያዊ አገልግሎት ላስ ቬጋስ ከተማ ገቡ።
ብጹእ አቡነ ቴዎፍሎስ ዶ/ር በነገው ዕለት በላስ ቬጋስ ከተማ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ለሚከበረው የቅዱስ ሚካኤል ዓመታዊ ንግሥ በዓል ላይ ለመገኘት ፣ በከተማው የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናትን ለመባረክ እንዲሁም ምዕመናንን ለማስተማር ዛሬ ከሰዓት ላስ ቬጋስ Harry Reid ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ደርሰዋል። መልአከ ሥብሃት ቆሞስ አባ ኃይለ ኢየሱስ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የደብሩ አስተዳዳሪ ከደብሩ ካህናት ጋር በመኾን በ Harry Reid ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በመገኘት አቀባበል አድርገውላቸዋል። በተመሳሳይ በማለዳ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ዶ/ር የኒውዮርክ እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ በዓሉን ለማክበር ላስ ቬጋስ ደብረ ምሕረት ቅ/ሚካኤል ደብር ደርሰዋል።

ለደብረ ምሕረት ቅ/ሚካኤል ቤ/ክርስቲያን ላስ ቬጋስ ሕንጻ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ
ብጹእ አቡነ ቴዎፍሎስ ዶ/ር የሰሜን ካሊፎርኒያ ኔቫዳ እና አሪዞና ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና ብጹእ አቡነ ጴጥሮስ ዶ/ር የኒውዮርክ እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ በአዲስ መልክ በኢትየኦጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ የሥነ ሕንጻ ዲዛይን ለሚገነባው የላስ ቬጋስ ደብረ ምሕረት ቅ/ሚካኤል ቤ/ክርስቲያን የመሠረት ድንጋይ አኖሩ።

የሰሜን ካሊፎርኒያ ኔቫዳ እና አሪዞና ሀገረ ስብከት ዓመታዊ ሪፖርት በ42 ኛው የኢት/ኦ/ተ/ቤ/ክ መንበረ ፓትርያርክ ዓለም አቀፍ አጠቃላይ የሰበካ ጉባዔ ስብሰባ
ሪፖርቱን ለማድመጥ Read More የሚለውን ሊንክ ይጫኑ

የሀገረ ስብከቱ ሦስተኛ ዓመታዊ አጠቃላይ ስብሰባ
ከነሐሴ ፳፮ እስከ ነሐሴ ፳፯ ፳፻፲፭ ዓ/ም / Sept 1 & 2 2023 በደብረ ሰላም ኢየሱስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ኦክላንድ ካሊፎርኒያ የተደረገው የሀገረ ስብከቱ አጠቃላይ ስብሰባ መግለጫ፤

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የገጠማትን ወቅታዊ ፈተና በተመለከተ ከሰሜን ካሊፎርኒያ ኔቫዳ እና አሪዞና ሐገረ ስብከት የተሰጠ መግለጫ
ህገ ወጥ እና ኢ-ቀኖናዊ የጳጳሳት ሹመት በተመለከተ ከሀገረ ስብከታችን የተላለፈውን መግለጫ ለማንበብ Read More የሚለውን ሊንክ ይጫኑ

የሰሜን ካሊፎርኒያ ኔቫዳ እና አሪዞና ሀገረ ስብከ ዓመታዊ ሪፖርት በ41 ኛው የኢት/ኦ/ተ/ቤ/ክ መንበረ ፓትርያርክ ዓለም አቀፍ አጠቃላይ የሰበካ ጉባዔ ስብሰባ
ሪፖርቱን ለማድመጥ Read More የሚለውን ሊንክ ይጫኑ

ብጹዕ አቡነ ቴዎፍሎስ የሰሜን ካሊፎርኒያ ኔቫዳ እና አሪዞና ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በዛሬው ዕለት በክሊኒካል ሳይኮሎጂ ዶክተር ኦፍ ሳይኮሎጂ ዲግሪ ተመረቁ።
በኢት/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያን የሰሜን ካሊፎርኒያ ኔቫዳ እና አሪዞና ሀገረ ስብከት ሊቀ ዻዻስ ብጹዕ አቡነ ቴዎፍሎስ በዛሬው ዕለት October 14 2022 እኤአ ከሰሜን ካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ በከፍተኛ የትምህርት ማዕረግ ውጤት (Magna Cum laude) በክሊኒካል ሳይኮሎጂ ዶክተር ኦፍ ሳይኮሎጂ ዲግሪ የተመረቁ ሲኾን በምርቃት መርሐግብሩ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ስብሃት ቆሞስ አባ ኃይለ ኢየሱስ ገሰሰ ፣ የሐገረ ስብከቱ ዋና ጸሐፊ ሊቀ ስዩማን ቀሲስ ቡሩክ አልዩ እንዲሁም የአድባራት አስተዳዳሪ ቆሞሳት እና የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻቸው ምእመናን ተገኝተው የእንኳን ደስ አለዎት የደስታ መግለጫቸውን አቅርበዋል። ብጹዕነታቸው በአመራር (leadership) ክህሎታቸው ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በተለያየ ከፍተኛ ኃላፊነት ያገለገሉ እና እያገለገሉ ያሉ ሲኾን ቤተ ክርስቲያን በፈተና ውስጥ ባለችበት ወቅት በተመደቡበት የአገልግሎት መስክ መንፈስ ቅዱስን በማስቀደም ውጤታማ ሥራ ያስመዘገቡ ናቸው። ከ 20 ዓመት በላይ በምንኲስና ማዕረግ ባገለገሉበት የሎስ አንጀለስ ጽርሀ ጽዮን ቅድስት ማርያም የኢት/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያን ካቴድራል የእንኳን ደስ አለዎት ሠፊ መርሀግብር የተዘጋጀ ሲኾን በዕለቱ ከደብሩ ሰበካ ጉባዔ ፣ ከመንፈስ ቅዱስ ልጆቻቸው እና ከደብሩ አገልጋይ ካህናት የእንኳን ደስ አለዎት ገጸ በረከት ተደርጎላቸዋል። በመርሐ ግብሩ የሀገረ ስብከቱ የደስታ መግለጫ እና ገጸ በረከትም የቀረበ ሲኾን የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ስብሃት ቆሞስ አባ ኃይለ ኢየሱስ ገሰሰ ባስተላለፉት መልዕክት የብጹዕነታቸው ምርቃት የቤተ ክርስቲያን ደስታ ነው ብለዋል። በመቀጠል ክቡር ሥራ አስኪያጁ እንዳስቀመጡት ብጹዕነታቸው በዘመናዊው የትምህርት ዓለም ቆይታቸውም ያሳለፉት ውጣ ውረድ እና ዕውቀታቸውን ከፍ ለማድረግ ያሳዩት ጥረት እና ያስመዘገቡት ውጤት ሀገረ ስብከቱን እና በየደረጃው ያሉ የሀገረ ስብከቱን ኃላፊዎች እንዲሁም የአጥቢያ አገልጋዮችን የሚያበረታታ ነው ብለዋል። ደስታው የቅድስት ቤ/ክርስቲያን ደስታ ስለሆነ ኦርቶዶክሳውያን እንኳን ደስ አለን።

የሀገረ ስብከቱ ሁለተኛ ዓመታዊ አጠቃላይ ስብሰባ
ከነሐሴ ፳፯ እስከ ነሐሴ ፳፰ ፳፻፲፬ ዓ/ም / Sept 2 & 3 2022 በደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላስ ቬጋስ የተደረገው የሀገረ ስብከቱ አጠቃላይ ስብሰባ መግለጫ፤

በዓለም አቀፍ ደረጃ ስለተከሰተው የኮሮና ቫይረስ አስመልክቶ ከሰሜን ካሊፎርኒያ ኔቫዳ እና አሪዞና ሀገረ ስብከት የተላለፈ የጥንቃቄ መልዕክት
ስለኮሮና ቫይረስ ከሀገረ ስብከቱ የተላለፈውን መልዕክት ለማንበብ Read More የሚለውን ሊንክ ይጫኑ

የሀገረ ስብከቱ የመጀመሪያ ዓመታዊ አጠቃላይ ስብሰባ
ከሚያዝያ ፬ እስከ ሚያዝያ ፭ ፳፻፲፩ ዓ/ም / April 12-13 2019 በመካነ ራማ ቅዱስ ገብርኤል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሳንሆዜ ካሊፎርኒያ የተደረገው የሀገረ ስብከቱ አጠቃላይ ስብሰባ መግለጫ፤
bottom of page



